ዝቅተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በገና በዓል ወቅት ከዋናው የኤሌክትሪክ ቋት ኃይል እንዳይጠቀሙ ተጠየቀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

ታኅሣሥ 26/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመጪው የገና በዓል ወቅት ሊኖር የሚችለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር ለመፍታት የተለያዩ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጿል።

አገልግሎቱ በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች በመለየት በመካከለኛና በዝቅተኛ መስመሮች ላይ ጭነት የማመጣጠንና ሌሎች የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ባወጣው በመግለጫ አንስቷል።

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመሆን በኃይል ማመንጫ፣ ማሰራጫ መስመሮች፣ ትራንስፎርመሮች እና በዝቅተኛ መስመሮች ላይ ብልሽቶች ሲያጋጥሙ በአፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ግብርኃይል በማቋቋም ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያለው፡፡

ከሲሚንቶ እና የኤክስፖርት ኢንዱስትሪዎች በስተቀር የድንጋይና እህል ወፍጮ፣ የፕላስቲክ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የኬሚካልና ሌሎች ዝቅተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የኃይል አጠቃቀማቸውን እንዲያስተካክሉ ገልጿል።

በዚህም መሰረት ኢንዱስትሪዎቹ በበዓሉ ዋዜማ ታኅሣሥ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 እስከ በዓሉ ዕለት ምሽት 4፡00 ድረስ ከዋናው የኃይል ቋት (ግሪድ) ኤሌክትሪክ ሙሉ ለሙሉ እንዳይጠቀሙና ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ተቋሙ ጠይቋል።

የቅድመ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞችም በዓሉ ሲደርስ የሚኖረውን አላስፈላጊ እንግልት ለማስቀረት የሚበቃቸውን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ አስቀድመው እንዲገዙ ወይም ካርድ እንዲሞሉ ተቋሙ አሳስቧል፡፡

ደንበኞችም በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሳቁስ ኃይል ቆጣቢና ለአደጋ የማያጋልጡ መሆን ይገባቸዋል ያለው ተቋሙ ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባሉት ጊዚያት ቢጠቀሙ የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያገኙ ጠቁሟል።

የኤሌክትሪክ አደጋ ቢያጋጥም፣ ተቋሙን የሚመለከቱ ሌሎች መረጃዎች ለመጠየቅ፣ ጥቆማዎችና አስተያየቶች ለማቅረብ ወደ አቅራቢያ የሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ ማሳወቅ ወይም ወደ 905 ነፃ የጥሪ ማዕከል መደወል እንደሚያስፈልግ የአገልግሎቱ መረጃ ያመለክታል፡፡