የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኤርትራ ጉብኝት እያደረጉ ነው

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ

ታኅሣሥ 27/2014 (ዋልታ) በአዲሱ ዓመት ቀዳሚ ጉዟቸውን ወደ አፍሪካ እንደሚያደርጉ አሳውቀው የነበሩት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ትናንት ምሽት ኤርትራ ገቡ።

ጉብኝታቸውን በአፍሪካ ቀንድ የጀመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስመራ ሲደርሱም የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በጉብኝታቸው ከኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር እንደሚወያዩ ደግሞ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል ጠቁመዋል።

ቻይና በምጣኔሃብት የጋራ እድገትና በእኩልነት ላይ በተመሰረተ ትብብር ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች ትገኛለች። ቻይና ለአፍሪካ የቀረጥ ነፃ የግብርና ምርቶች ገበያን ማመቻቸቷንም በቅርቡ አሳውቃ ነበር።

ኤርትራ የሚገኙት የቻይናው ባለሥልጣን ከወር በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች እንዲሁም ኢትዮጵያ ወቅታዊ ፈተናዋን በራሷ አቅም እንደምትወጣው መነጋገራቸው ይታወሳል።

በወቅቱም ቻይና በሉኣላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንደማትቀበል መግለፃቸው አይዘነጋም።

በተናጠል አገራትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያ ላይ ጫና የማሳደሪያ ስብሰባዎችንና የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉም ቻይና ስትቃወም ከርማለች።