ሁዋዌ ኢትዮጵያ ለምታዘጋጀው ዓለም ዐቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ድጋፍ አደርጋለው አለ

ታኅሣሥ 27/2014 (ዋልታ) ሁዋዌ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት የምታዘጋጀውን ዓለም ዐቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ በገንዘብና በቴክኒክ እንደሚደገፍ የግሩፑ ምክትል ስራ አስፃሚው ቻርለስ ዲንግ ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ከሁዋዌ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ቻርለስ ዲንግ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍም ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ ምክትል ስራ አስፃሚው በውይይታቸው ወቅት ገልጸዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ሁዋዌ ዓለም ዐቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ዝግጅትን ለመደገፍ ቃል በመግባቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሁዋዌ የቴክኖሎጂ ግሩፕ በዓለም ላይ ካሉት ሰራተኞቹ ውስጥ ኢትዮጵያውያን በጣም ጥቂት ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያውያንን ማሳተፍ ላይ በትኩረት እንዲሰራም ጠይቀዋል።

ሁዋዌ የቴክኖሎጂ ግሩፕ በዓለም ላይ ከ197 ሺሕ በላይ ሰራተኞች ያለው ሲሆን አፍሪካ ውስጥ ካሉት 8ሺሕ 600 ሰራተኞች ውስጥ 76 ከመቶ አፍሪካውያን ሲሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሰራተኞች ውስጥ 80 ከመቶዎቹ የሀገር ውስጥ ሰራተኞች መሆናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡