የገና እና ጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ከወጣቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው

ታኅሣሥ 27/2014 (ዋልታ) የገና እና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ፖሊስ ከወጣቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ፖሊስ ከከተማዋ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ጋር በመቀናጀት የመዲናዋን ሰላም እያስጠበቀ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ዲያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመዲናዋ የትኛውም አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የጸጥታ ችግር እንዳይገጥማቸው ፖሊስ የተጠናከረ ክትትልና ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡