በአሸባሪው ቡድን የወደሙ የጤና ተቋማት እየተሰነዱ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

ጥር 12/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የወደሙ የጤና ተቋማትን በመሰነድ ለዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ እየተሠራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደገለጹት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጦርነት በጤና ተቋማት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ውድመት ደርሷል።

አንዳንድ የምዕራባውያን መንግሥታት፣ ሚዲያዎችና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ውድመቱን ለማወቅና ለመረዳት ቸልተኝነት ቢታይባቸውም ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ለማሳወቅ የጤና ሚኒስቴር ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን በጥናት የወደሙትን የጤና ተቋማት የመለየትና የመሰነድ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

ቡድኑ በጤና ተቋማት ላይ ያደረሰውን ውድመት የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም ዐቀፍ ረጂ ድርጅቶች አላወገዙትም ያሉት ዶክተር ደረጀ እነዚህ ተቋማት የሚያደርጉት እገዛ አነስተኛ በመሆኑ በራስ አቅም በተጀመረው መንገድ ለዓለም ማሳወቅና መልሶ ለመገንባት መሥራት ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።