የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት

ጥር 12/2014 (ዋልታ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎችም እንደሚከተለው ቀርበዋል።

  1. ምክር ቤቱ በቀዳሚነት የተወያየው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትን አደረጃጀት፣ ስልጣን እና ተግባራቱን ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ሥራን በተቀናጀና በተናበበ አኳኋን በማከናወን ብዙኃኑን ተደራሽ የሚያደርግና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ባማከለ መንገድ ትክክለኛ መረጃን ተቋማዊ በሆነ መንገድ ማድረስ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ እንዲሁም ዜጎችን በሀገራዊ ልማትና በአካታች የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በብቃት ለማሳተፍና ለአዲሱ ምዕራፍ ጉዞ፣ ለሀገራዊ ለውጦችና ብልጽግና ስኬት ተገቢውን ሚና መጫወት እንዲችሉ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ የአገልግሎቱን አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር የሚወስን ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በስፋት ተወያይቶ ከዛሬ ጥር 12 ቀን 2014 ዓም ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

  1. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በመንገድ ትራንስፖርት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የበለጠ ለማጎልበት ዘርፉ አስተማማኝ፣ የተቀናጀ፣ ዘመናዊና ደህንነቱ የተረጋገጠ ሆኖ እንዲራመድ ማድረግ በማስፈለጉ፣ እንዲሁም የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎትን አስመልክቶ የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት ተግባሮቻቸውን ተናበውና ተቀናጅተው በውጤታማነት መፈጸም የሚያስችላቸው የህግ ማእቀፍ በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

  1. የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎትን ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅ ደንብ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ ነው፡፡ የመንገድ ደህንነት ሥራዎችን የሚመራ ጠንካራ መዋቅራዊ አደረጃጀት አለመኖሩ በሀገራችን ጎልተው ለሚታዩት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ችግሮች አንዱ መንስኤ መሆኑ ስለታመነበት፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የመንገድ ደህንነት ተግባራት በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እና በተለያዩ የትራንስፖርት መዋቅሮች የተበታተኑ በመሆኑ ባልተቀናጁ እቅዶች እንዲመራ መደረጉ ውጤታማ ሊያደርገው ባለመቻሉ፣ እንደዚሁም በተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ የነበረው የመንገድ ደህንነት አደረጃጀትም ቢሆን ምክር ከመስጠትና ግንዛቤ ከመፍጠር የዘለለ ድርሻ ያልነበረው ከመሆኑ አንጻር በመንገድ ደህንነት ረገድ የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉ ለደንቡ መሻሻል ምክንያት ሆኗል፡፡ ስለሆነም በመሰረታዊነት የዘርፉን ችግር መፍታት እንደሚያስችል የታመነበት ረቂቅ ደንብ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ ተወያቶ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

ቀጥሎ ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው በአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ረቂቅ ደንብ ላይ ሲሆን የተሳለጠና ደህንነቱ የተረጋገጠ የመንገድ ትራንስፖርት እንዲኖር ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የአሽከርካሪዎች የማሽከርከር ብቃት ስለሆነ ብቃት ያላቸውን አሽከርካሪዎች ለማፍራት የማሽከርከር ብቃት ማረጋገጫ ስርዓት መቅረጽና የህግ እውቅናና ድጋፍ መስጠት የሚገባ በመሆኑ እንዲሁም ከብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸውን አካላት ተግባርና ሃላፊነት በግልጽና በዝርዝር መደንገግ በማስፈለጉ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ ተወያይቶግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

  1. ምክር ቤቱ የባለሞተር ተሽከርካሪዎች የፍጥነት ወሰን ረቅቅ ደንብ ላይ የተወያየ ሲሆን የተሽከርካሪ ፍጥነት ዋነኛ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መንስኤ እንደመሆኑ ለችግሩ ተገቢው መፍትሄ ካልተበጀለት በፍጥነት ምክንያት እየደረሰ የሚገኘውን ከፍተኛ የሆነ የሰው ሕይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት መቀነስ የማይቻል በመሆኑ፤ በ1961 ዓ.ም የወጣው የተሽከርካሪዎች የፍጥነት ወሰን ደንብ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የትራፊክ ፍሰት፣ የመንገድ እድገት እና የአሽከርካሪዎች ባህሪ ለማረቅና ለመምራት የሚያስችል ባለመሆኑ ከጊዜው ጋር የሚራመድ የህግ ማእቀፍ በማስፈለጉ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጀቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
  2. በመቀጠል ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው የአሽከርካሪ ክብደትና መጠንን ለመወሰንና ለመቆጣጠር በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ ሲሆን የሀገራችንን የኢኮኖሚ እድገት ለመደገፍ የትራንስፖርት ዘርፍ አስተዋጽ ከፍተኛ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሽከርካሪዎች መጠንና የመጫን አቅም ከፍ እያለ በመሄዱ የመንገዶቻችንን ደረጃ መሰረት በማድረግ በመንገዶች ላይ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ክብደት እና መጠን በመወሰን በመንገዶች ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ጉዳትና ብልሽት ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት፤ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ላይም ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ለማስወገድ እንዲሁም በሀገራችን በፍጥነት እያደገ የመጣውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ይቻል ዘንድ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
  3. ቀጥሎ ምክር ቤቱ የተወያየው የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ሲሆን የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲቋቋም ዋና አላማው የነበረው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚኖሩ የፌዴራል መንግስትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲሁም ከስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ውጭ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በአነስተኛ ታሪፍ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ነበር፡፡ የአገልግሎቱን ተደረሽነት በማስፋት ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሙሉ ቀን አገልግሎት መስጠት እንዲቻል በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች እየኖሩ በፌደራል መንግስት እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት የሚያገለግሉ ሰራተኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ ደንብ ቁጥር 298/2006ን የሚያሻሽል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
  4. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትን ማጠናከር በሀገሪቱ ከፋይናንስ እንቅስቃሴ እድገትና ከቴክኖሎጂ መዘመን ጋር እየተሳሰሩ የመጡትን የፋይናንስ ወንጀሎችን በተለይም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እንዲሁም ሽብርተኝነትን እና የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ብዜት በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል እንዲሆን፤ በተጨማሪም ሀገራችን ከተቀበለቻቸው እና ካጸደቀቻቸው ከዓለም አቀፍ የትብብር ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ ዓለም ዓቀፋዊና አህጉራዊ ትስስር በመፍጠር የወንጀል መንስኤዎችን፣ ስጋቶች እና ድርጊቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል የህግ እና የአሰራር ክፍተቶችን መሙላት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ ተወያይቶ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡