አሸባሪው ሕወሓት ግጭቱን ለመቀጠል ባለው ፍላጎት አሁንም ትንኮሳውን እንደቀጠለ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ

ጥር 13/2014 (ዋልታ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ክልላዊ ዳይሬክተር ሚካኤል ጆን ደንፎርድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በወቅቱም አሸባሪው የትሕነግ ቡድን በአፋር እና አማራ ክልሎች በፈጸመው ወረራ በርካታ የሰብኣዊና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን አስረድተዋቸዋል።
መንግሥት በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ያለው ግጭት እንዲቆም ባለው ፍላጎት ሰራዊቱን ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ መወሰኑን ያብራሩት አምባሳደር ሬድዋን ነግር ግን የሽብር ቡድኑ አሁንም ግጭቱን ለመቀጠል ባለው ፍላጎት የተነሳ ትንኮሳውን እንደቀጠለ ገልጸዋል።
የሰብኣዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል የገቡ ተሽከርካሪዎችን ትሕነግ ለሰራዊቱ ማጓጓዣነት ማዋሉን አስታውሰው ተሽከርካሪዎቹ መመለስ እንዲችሉ መንግሥት ሁኔታዎችን ያመቻቸ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰቡ ጉዳዩን በዝምታ በማለፉ በክልሉ የሰብኣዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ ችግር መፍጠሩን አንስተዋል።
መንግስት የፍተሻ ኬላዎች ቁጥርን በመቀነስ፣ የሰብኣዊ እርዳታ በማቅረብ የተሰማሩ ድርጅቶች ወደ ክልሉ ይዘውት የሚገቡትን የጥሬ ገንዘብ መጠን በማሳደግ እንዲሁም በአየር የሚደረጉ የሰብኣዊ እርዳታ በረራዎችን መጠን በጨመር ቁርጠኝነቱን ማረጋገጡን አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊት ያለበት በመሆኑ አሸባሪው ኃይል ትንኮሳውን እስካላቆመ ድረስ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የሚወሰዱ እርምጃዎች ንጹሃንን ዒላማ ያደረጉ ናቸው በሚል ከቡድኑ የሚወጡ መረጃዎች ተጨባጭነት የሌላቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ክልላዊ ዳይሬክተር ደንፎርድ በበኩላቸው መንግሥት ለተከተለው የሰላም መንገድ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው በአንጻሩ ሕወሓት በአብአላ በኩል የከፈተው ጥቃት ችግሩን እያወሳሰበው መሆኑን አንስተዋል።
ድርጅታቸው 700 ቶን የምግብ እርዳታ አቅርቦት ለማድረግ መዘጋጀቱን ጠቁመው በአፋር እና አማራ እርዳታ ለሚሹ ወገኖችም ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ፣ ኬንያና እና ሶማሊያ የድርቅ ተጎጂዎችን ለመርዳት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጥረት እያደረገ መሆኑን መግለጻቸውን የወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መረጃ አመልክቷል።
በመጨረሻም አሸባሪው ትሕነግ የሰላም አማራጮችን ወደ ጎን በመተው ለሚያደርገው ግጭትን የማስፋፋት ተግባር የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ተጠያቂ ሊያደርገው እንደሚገባ በውይይታቸው ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።