አሸባሪው ትሕነግ በደቡብ ወሎ ከ548 በላይ ንፁሃንን ሲገድል ከ217 በላይ ሴቶችን መድፈሩ ተረጋገጠ

ጥር 13/2014 (ጥር) አሸባሪውና ወራሪው የትሕነግ ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን ከ548 በላይ ንፁሃንን በጅምላ ሲገድል ከ217 በላይ ሴቶችን መድፈሩን በመጀመሪያ ዙር የዳሰሳ ጥናት እንዳረጋገጠ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
አሸባሪው ቡድን አካባቢውን በወረረበት ወቅት ከ217 በላይ ሴቶች መድፈሩ በዳሰሳ ጥናቱ መረጋገጡን ነው የዞኑ አስተዳዳሪ አብዲ ሁሴን (ዶ/ር) የገለጹት፡፡
የጥቃቱ ሰለባዎችም ከ8 ዓመት ህፃናት እስከ አረጋውያን ሴቶች መሆናቸውንም ገልፀዋል።
ቡድኑ ከ548 በላይ ንፁሃንን መግደሉን በጥናቱ ደርሰንበታል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ በዞኑ በርካታ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውንም አሳውቀዋል።
ጥናቱ የመጀመሪያ ዙር መሆኑን የጠቆሙት አስተዳዳሪው የጥቃቱ ሰለባዎች ቁጥር ከተጠቀሰው ሊያሻቅብ እንደሚችል መናገራቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል።