በአሸባሪው ሕወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መልሶ ለመገንበት የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል – ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ጥር 15/2014 (ዋልታ) በምሥራቅ አማራ በሕወሓት የሽብር ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለማነቃቃትና ወደ ሥራ ለማስገባት ከባለሃብቶችና አጋር አካላት ጋር በደሴ ከተማ ምክክር እየተደረገ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) እንደተናገሩት አሸባሪው የትሕነግ ቡድን በክልሉ በፈፀመው ወረራ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ደርሷል።

እንዲያም ሆኖ ከጉዳቱ ለማገገም የወደመውን ሃብት ለመገንባት በቁጭት መነሳት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለዚህም የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት፣ ከዳያስፖራ ማኅበረሰብና ከሕዝብ ጋር በመሆን በአሸባሪ ቡድኑ የወደመውን ለመተካት ርብርብ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የወደሙ ፕሮጀክቶች ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ የብዙ ባለድርሻ አካላት እገዛ እንደሚያስፈልግ ነው ርእሰ መሥተዳድሩ የጠቆሙት።

“ሁላችንም የጋራ ቅንጅት በመፍጠር የበኩላችንን እንወጣ” ሲሉም መልዕክት ማስተላለፋቸውን አሚኮ ዘግቧል።

በመድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እና የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።