ኮሚሽኑ ለኮንሶ ዞን ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ጥር 16/2014 (ዋልታ) የጉምሩክ ኮሚሽን በኮንሶ ዞን በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች 24 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ምግብ ነክ ቁሳቁስ እና የግንባታ እቃዎችን ድጋፍ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ በመንግስት ከተሰጠው ገቢን በብቃት የመሰብሰብ፣ የወጭና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ማድረግ፣ ህገ ወጥ ንግድን እና ኮንትሮባንድን ከመከላከል ተልእኮው በተጨማሪ ማኅበራዊ ግዴታውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ድጋፉን ያስረከቡት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በኮንሶ ዞን በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም 24 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ምግብ ነክ ቁሳቁስ፣ አልባሳት እና የግንባታ እቃዎች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ጊዚያት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ድጋፎቹ በተለያዩ ጊዜያት የህይወት እና የአካል መስዋዕትነት ተከፍሎባቸው የተያዙ የኮንትሮባንድ እቃዎች በመሆናቸው ለተጎጅዎች በትክክል እንዲደርሱም ኮሚሸነር ደበሌ አሳስበዋል።

የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው በዞኑ በሰው ሰራሽ ችግሮች የተፈናቀሉ ከ80 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መኖራቸውን ገልጸው በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ እንደሆነ ማስረዳታቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።