በምስራቅ ወለጋ በሸኔ የሽብር ቡድን 6 ግለሰቦች መታገታቸውንና ለማስለቀቅ እየሰራ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ

ጥር 16/2014 (ዋልታ) ሸኔ አምስት ተማሪዎችንና አንድ በንግድ ሥራ የሚተዳደር ግለሰብን ጨምሮ 6 ሰዎችን በኦሮሚያ ክልል ማገቱን የፌደራል የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
ግብረ ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ ታጋቾቹ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ሲጓዙ ምስራቅ ወለጋ ጎቡ ሰዮ ወረዳ ልዩ ስሙ ባፋኖ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ጥር 15 ቀን 2014 ከቀኑ 10 ሰአት አካባቢ በሽብር ቡድኑ ታፍነው መወሰዳቸውን ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።
ከሽብርተኛው ሕወሓት ጋር በመቀናጀት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሽብርና ትርምስ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱት የሸኔ ቡድን ታጣቂዎች በፌደራል የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እና በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት በቅንጅት እየተወሰደባቸው ባለው እርምጃ እየተደመሰሱ መሆናቸውን መግለጫው ጠቁሟል።
ይሁንና የተበታተኑት የቡድኑ አንዳንድ ኃይሎች በየዋሻውና ጥሻው በመደበቅ በንፁሃን ላይ አስነዋሪ አፈናና እገታ መፈፀማቸውን ነው በመግለጫው ያመለከተው፡፡
ታጋቾችን የማስለቀቁ እንቅስቃሴም እየተካሄደ በመሆኑ፤ እርምጃዎችን ተከትሎ የሚገኘውን ውጤት በቀጣይ ለሕዝቡ እንደሚያሳወቅ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦