የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቋማዊ ነፃነት እንዲሳካ ለማገዝ የተደራጀው ግብርኃይል ወደ ሥራ ገባ

ጥር 19/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነፃ እና ራሱን የቻለ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ የተደራጀው ግብርኃይል ወደ ሥራ መግባቱ ተገለፀ።

የትምህርት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ጋር የግብርኃይሉን የሥራ ማስጀመሪያና ትውውቅ መድረክ አካሂዷል፡፡

መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነት ተጎናፅፈው መሥራት እንዲችሉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ነፃነት ኖሮት መልሶ እንዲደራጅ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

በውይይቱም የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቋማዊ ነጻነት መስጠት ከመንግሥትም ከማኅበረሰቡም ስምምነት የተደረሰበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህ የለውጥ ሥራ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቃማዊ ነጻነትን ማምጣት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተቋማዊ ነጻነት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነፃነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ከፍተኛ ተቋማትም የሚስፋፋ መሆኑም ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ፣ የማኔጅመንት አባላት እና የተመረጡ ግብርኃይሉ አባላቶች መሳተፋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።