አሸባሪው ሕወሓት በኮምቦልቻ ከተማ ያወደማቸው መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ዳግም ማምረት ጀመሩ

ጥር 20/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት በኮምቦልቻ ከተማ ዘረፋና ውድመት የፈፀመባቸው አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በመልሶ ግንባታ የማምረት ሥራ መጀመራቸውን የከተማው ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አባይነህ አበባው የሽብር ቡድኑ በከተማዋ በቆየባቸው ጊዜያት በ23 ከፍተኛ፣ 9 መካከለኛና 25 አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ዘረፋና ውድመት አድርሷል ብለዋል።

በኢንዱስትሪዎቹ ላይ በጥቅሉ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን በኢንዱስትሪዎቹ ላይ ባደረሰው ጥፋት ከ6 ሺሕ በላይ ሰራተኞች ከሥራ ውጭ ሆነው መቆየታቸውን ጠቅሰው አሁን ወደ ሥራ በመመለስ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎቹ በመልሶ ግንባታና ድጋፍ ታግዘው ወደ ማምረት ሥራ መግባታቸውን ነው የገለጹት።

ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ በተለይም የኃይል አቅርቦትና ሌሎችም ችግሮች በመፈታት ላይ እንደሆኑ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኮምቦልቻ ከተማ 179 የተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።