አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ኢትዮጵያ በውጭና በውስጥ ኃይሎች የተደቀነባትን የኅልውና አደጋ አክሽፋለች አሉ

ጥር 21/2014 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ኢትዮጵያ በውጭና በውስጥ ኃይሎች የተደቀነባትን የኅልውና አደጋ ማክሸፏን ገለፁ።

ለሁለት ቀናት የሚቆይ አገር ዐቀፍ የህግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው።

አፈ ጉባኤው ዛሬ የህግ አውጭዎች መድረኩ በስኬትና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲካሄድ  የሀገራችንን ኅልውና ላስከበሩ ጀግኖች የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ምስጋና ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው በፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት መድረክ መርህ አልነበረውም ነው ያሉት።

በገዥው የፖለቲካ ፓርቲ አሠራር ላይ የተመሠረተ እና ለመንግሥታት ነፃ አሰራርን ዋስትና የማይሰጥ እንደነበርም አንስተዋል።

ይህንን አሰራር ለመቀየርም በ2013 የፌዴራልና የክልል መንግሥታትን ግንኙነት የሚወስን አዋጅ መፀሰደቁን አስታውሰው አዋጁ ከፀደቀ በኋላ የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የህግ አውጭዎች የግንኙነት መድረክ ዛሬ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

በአዋጅና በመርህ ላይ የተመሠረተው ይህ የግንኙነት መድረኩ የተናበበ እቅድ እንዲኖር ሀገራዊ ፖሊሲዎችን በስኬታማነት ለማስፈፀም ያስችላል ነው ያሉት።

የጋራ የግንኙነት መድረኮች በዓለም የፓርላማ ኅብረትም የተለመደ አሠራር መሆኑን ጠቅሰዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።