ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን አንድነታችንን አጠናክረን ለመልሶ ግንባት በጋራ መቆም አለብን አሉ

ጥር 21/2014 (ዋልታ) ‘አንድነታችንን አጠናክረን ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት በጋራ መቆም አለብን’ ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ።
የገቢዎች ሚኒስቴር በ2013 የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።
በዚህ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን አገራዊ አንድነት በመገንባትና የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በማስጠበቅ ረገድ ሁላችንም በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሙሉ ለሙሉ ቆመዋል ማለት አይቻልም ያሉት ሚኒስትሩ አሁንም አንድነታችንን በማጥበቅ ለበለጠ ድል የምንሸጋገርበት ጊዜ መሆን አለበት ብለዋል።
በተለያየ አውድና መንገድ በጠብ አጫሪነት፣ በአቀነባባሪነትና አሳዛኝ የሆኑ ጥፋቶችን ለማስቀጠል የተዘጋጁ ኃይሎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።
እነዚህን የጥፋት ዓላማ ያነገቡ ኃይሎች በዘላቂነት ለመመከትና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት አንድነትና የጋራ አሸናፊነታችን መቀጠል አለበት ብለዋል።
በአገር ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እንዳይደገሙ በማክሸፍ ስጋት እንዳይሆኑ መመከት ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ የደረሱ ጉዳቶችን መልሶ የማልማትና የመገንባት ጉዳይም የጋራ ተግባራችን መሆን አለበት ነው ያሉት።
በዜጎች ላይ የደረሱ ስብራቶችን የመጠገንና መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለአገልግሎት በማብቃት ሥራ ላይ እንረባረብ ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።