በአማራ ክልል የሚገኙ የልማት ድርጅቶች በኅብረት ሊቆሙ ይገባል ተባለ

ጥር 21/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል “የግብርና ቤተሰብ” የልማት አጋር አካላት የአሠራር ግንኙነት መድረክ የምስረታ ጉባኤ ተካሄደ።
በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ የልማት ድርጅቶችን በማቀናጀት ምርታማነት ማሻሻል እንዲቻል የልማት አጋር አካላት “የግብርና ቤተሰብ” መመሥረት አስፈላጊ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ/ር) በክልሉ በተለያየ አካባቢ የሚገኙ የግብርና አጋር አካላትን ድጋፍ እና ክትትል ለማድረግ ያመች ዘንድ ወደ አንድ በማሰባሰብ የግብርና ቤተሰብ መመሥረቱን ተናግረዋል።
የግብርና ቤተሰብ መመሥረቱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ልምድ ለመለዋወጥ እና ያሉበትን የአካባቢ ሥርጭት በመለየት በተጠቃሚዎች የሚነሳውን የፍትሐዊነት ጥያቄ ለመመለስ እንደሚያመችም ጠቁመዋል።
በክልሉ ካሉ 167 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ 36ቱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከግብርና ጋር የሚሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ባሕር ዳር ፊልድ ኦፊስ የአቅም ግንባታ አመቻች ኦፊሰር አዱኛ ገላ (ዶ/ር) በበኩላቸው የማኅበረሰቡን የመልማት ጥያቄ የሚመልሱ እና በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ውድመት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ በጋራ መሥራት ይገባል ማለታቸውን አሚኮ ነው የዘገበው፡፡