በተለያዩ የዓለም ሀገራት በተካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊ ሆኑ

ጥር 23/2014 (ዋልታ) በሣምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በተካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል፡፡

በጀርመን ካርልስሩህ የዓለም የቤት ውስጥ ቱር ውድድር በ3000 ሜትር በሪሁ አረጋዊ አንደኛ ደረጃን ሲይዝ በሌላ በኩል ደግሞ በጣሊያን ቪቶሬ ኦሎና በተደረገ ቺንኩ ሙሉኒ አገር አቋራጭ ውድድር በወንዶች ንብረት መላክ አንደኛ፣ ታደሰ ወርቁ ሶስተኛ፣ ቢቂላ ታደሰ ደግሞ አራተኛ ሆነው ውድድሩን ማጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

በስፔን ሲቪላ በተደረገ የግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶች ገብሬ እርቅይሁን ሶስተኛ ደረጃን ሲይዝ በተመሳሳይ በስፔን ጌታፌ በተደረገ የግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶች ሀብታሙ ብርሌው ሁለተኛ፣ ስንታየሁ ድንቄሳ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ወጥተዋል፡፡

በዚህ መርሃ ግብር በሴቶች ቤተልሔም አፈንጉስ አንደኛ እንዲሁም ብርቱካን ወርቅነህ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቃቸውን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡