ዩ ኤስ ኤድ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሰብኣዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ

ጥር 23/2014 (ዋልታ) የአሜሪካ ዓለም ዐቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤድ) በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሰብኣዊ ድጋፍና የልማት ፕሮግራም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ።
በኢትዮጵያ የድርጅቱ ዳይሬክተር ሲን ጆንስ ላለፉት በርካታ ዓመታት ዩ ኤስ ኤድ በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ተኮር የልማት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
በተለይም እናቶችና ህፃናት ሞት ቅነሳ፣ በትምህርት፣ በዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ፣ በጤና እና በንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ በግብርና፣ በምግብ ዋስትና ፕሮግራሞችና በሌሎችም መሰል ሰብኣዊ ድጋፎችና የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ሁነኛ አጋር ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል፤ አሁንም ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመትም በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተባቸው ደቡብ ኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል እና በደቡብ ሶማሌ አካባቢዎች ድጋፍ ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
በአማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች እርዳታ ለሚሹ ሰዎች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው በልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚኖረውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
“አሜሪካ ጠንካራና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት ትፈልጋለች” ሲሉም ተናግረዋል።
ዩ ኤስ ኤድ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከሰብኣዊ ድጋፎች በተጨማሪ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን የማከናወን እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚ፣ ጤና፣ ዴሞክራሲና በሌሎችም መስኮች በትብብር እንሰራለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በመመደብ ግብርናን በማሻሻል፣ የእናቶችና ህጻናትን ጤና በመጠበቅ፣ የገበያ ሁኔታን ማሻሻልና ሌሎችም የተፈጥሮ ሃብት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚተገበር ፕሮጀክት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚህ መርሃ ግብርም ከ1 ነጥብ 2 እስከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።