የተባበሩት መንግሥታት በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል የበኩሉን እንደሚወጣ ገለጸ

ጥር 24/2014 (ዋልታ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተደድር ሙስጠፌ መሀመድ በተባበሩት መንግሥታት የፕሮጀክት አገልግሎት ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ናእ የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ ወርቅነሽ መኮንን የተመራ የልዑካን ቡድን ጋር በክልሉ በተከሰተው የድርቅ ሁኔታ ዙሪያ ተወያይተዋል።
በዚህም ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ስለተከሰተው ድርቅ ሁኔታ እና የድርቁ አደጋ በዜጎች ህይወት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል የተያዙት እቅዶችና እስካሁን የተወሰዱ እርምጃዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት በተባበሩት መንግሥታት የፕሮጀክት አገልግሎት ቢሮ ዋና ዳይሬክተርና የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ ወርቅነሽ መኮንን በበኩላቸው ተቋማቸው በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ ለመታደግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡