አፍሪካ በመሪዎቹ ጉባኤ ጠንካራ አቋም መያዝ እንዳለባት ተገለፀ

ጥር 24/2014 (ዋልታ) አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ ጠንካራ አቋም መያዝ እንዳለበት የአብን የቀድሞው ሊቀመንበር እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የዓለም የፀጥታ፣ የምጣኔሃብትና የማኅበራዊ ጉዳዮች ውሳኔ በሚተላለፍበት በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
በመሆኑም በመጪው ቅዳሜና እሁድ በሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ጠንካራ አቋም መያዝ እንዳለበት በርካቶች ይገልፃሉ።
አፍሪካ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ገደማ ሕዝብ እየኖረባት በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ወኪል እንዳይኖራት መደረጉ በየትኛውም መመዘኛ ትክክል አለመሆኑን የምክር ቤት አባሉ ደሳለኝ ይናገራሉ።
በጥቂት ኃያላን ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የሚዘወረውን የዓለም ፖለቲካ ፈር ለማስያዝ አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባልም ይላሉ።
በመሆኑም በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ ጠንካራ አቋም ሊያዝ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።