ለአፍሪካዊ ችግሮች በፓን አፍሪካኒዝም የተቃኘ ኅብረትና የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ

ጥር 27/2014 (ዋልታ) ወቅታዊ የአፍሪካ ችግሮችን ለመፍታት በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ መሰባሰብና ለጋራ ጉዳዮች በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ዲፕሎማቶች ገለፁ።
ዲፕሎማቶቹ ፓን አፍሪካኒዝም መላው አፍሪካዊ አንዱ ለሌላው የቆመና ተቀራራቢ ታሪክ፣ ባህልና ተመሳሳይ ችግሮች ያሉበት ሕዝብ መሆኑን አመላካች አስተሳሰብ ነው ብለዋል።
በዚህ አስተሳሰብ በመቃኘትም አኅጉሪቱ ከኮሮና ቫይረስ፣ ከጸጥታ መደፍረስ ጀምሮ የሚፈትኗትን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
የዛምቢያው ዲፕሎማት አንድሪው ሲሉሜሲ (ዶ/ር) ፓን አፍሪካኒዝም አፍሪካዊያኖች አንድ መገኛ ያላቸው መሆኑንና እጣፈንታቸውን በጋራ ሊወሰን የሚችል መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
በተጨማሪ አፍሪካዊያን በዓለም ዐቀፍ መድረክ ላይ ያላቸውን ሥፍራ የሚያመላክትና በጋራ በመሥራት የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ የሚያነሳሳ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ኮቪድን ጨምሮ አፍሪካ የሚያጋጥማትን ችግሮች ለመፍታት በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኘ አጋርነትና አንድነት በመፍጠር ለጋራ ዓላማ መረባረብ እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡
ደቡብ ሱዳናዊው ዲፕሎማት ጆን ዮሄንስ በበኩላቸው ፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካ ሕዝቦች በተለያዩ አኅጉራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲቆሙና ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያደርግ እሳቤ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት አኅጉሪቱን በተለያየ መልኩ እየፈተኑ ያሉትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት በጋራ መረባረብ እንደሚገባም ነው የገለጸው፡፡
ወጣቶችን ተሳታፊ የሚያደርግ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲጠናከር ማድረግ እንደሚገባም ዲፕሎማቶቹ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡