ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅና የመንግሥታቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ በሶማሌ ክልል ውስጥ የተፈናቀሉ ወገኖችን ጠየቁ

ጥር 30/2014 (ዋልታ) ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሃመድ በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ቀብሪ በያህ ወረዳ መረጋቾ ቀበሌ የሚገኙ ዜጎችን ጎበኙ።
በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የተመራው ልዑክ በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች የሚገኙበትን ሁኔታ በመመልከት ተጎጂዎችን አፅናንተዋል።
የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሁመድ እና ሌሎች የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለልዑኩ በክልሉ ስለተከሰተው ድርቅና ስላደረሰው ጉዳት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም በድርቁ የተጎዱ ዜጎችና እንስሳትን ህይወት ለመታደግ የበለጠ ጥረትና ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በበኩላቸው በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ በአጭርና በረጅም ጊዜ ስልታዊ እቅዶች በመንደፍ መቅረፍ እንደሚቻል መጠቆማቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።