በምዕራብ ጎንደር ዞንና ደብረ ብርሃን ከተማ በኅልውና ዘመቻ ለተሳተፉ ዘማቾች የእውቅና ፕሮግራም ተካሄደ

የካቲት 1/2014 (ዋልታ) የምዕራብ ጎንደር ዞንና ደብረ ብርሃን ከተማ በኅልውና ዘመቻ ለተሳተፋ ዘማቾችና ለዘማች ቤተሰቦች የእውቅናና ምስጋና ፕሮግራም አካሄደ፡፡

ምዕራብ ጎንደር ዞን በተካሄደው ፕሮግራሙ ዘማቾች፣ የዘማች ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በኅልውና ዘመቻው ለቆሰሉ እና መስዋዕት ለከፈሉ ዘማቾች ምስጋና እና እውቅና ተሰጥቷል።

በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደሳለኝ ጣሰው አሸባሪው የትሕነግ ኃይል የአማራን ሕዝብ ለማጥፋትን ኢትዮጵያን ለመበተን የከፈተብንን ወረራ ለመመከት የአማራ ሕዝብ የማይተካ ሚና መጫውቱን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ጠላት የከፈተውን ጥቃት ለመመከት መከላከያ፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖዎች ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ጠላትን ደምስሰዋል፤ የተረፈውንም አሳፍረው መልሰዋል ብለዋል።

በዚህም ለፀጥታ ኃይሎችና ለጸጥታ ኃይሎች ደጀን በመሆን የድርሻቸውን ለተወጣው ሕዝቡ ምስጋና ይገባዋል ማለታቸውን ከምዕራብ ጎንደር ዞን ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ በደብረ ብርሃን ከተማ በኅልውና ዘመቻ ለተሳተፉ የጸጥታ አካላት የክልል፣  የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች በተገኙበት የዕውቅና እና የምስጋና መርሃግብር እየተካሄደ ይገኛል።

የምስጋናና እውቅና አሰጣጥ መርሃግብሩ በኅልውና ዘመቻው አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጸጥታ አካላትን፣ የመንግሥትና የግል ተቋማትን፣ ቀበሌ አስተዳደሮችንና ግለሰቦችን ያካተተ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።