ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ጸሀፊ ጋር ተወያዩ

ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

የካቲት 1/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሀመድ ጋር ተወያይተዋል።

በወቅቱም ዋና ጸሀፊዋ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ጫናዎችን ውስጥ እያለፈ እንኳ ሁኔታዎችን በሰከነ ሁኔታ በመመልከት ከተባበሩት መንግስታት ጋር ያለውን ግንኙነት ገንቢ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል ላሳየው ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ለመታደም መምጣታቸውን በሀገሪቱ የአማራ፣ ሶማሌና ትግራይ ክልሎች ጉብኝት በማድረግ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመገንዘብ ዕድል እንደፈጠረላቸውም አመላክተዋል።

በጉብኝታቸው በአካባቢዎቹ በተከሰቱ ግጭቶች የደረሰውን ሰብኣዊና ቁሳዊ ውድመቶችን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ በኅብረተሰቡ ላይ ያደረሰውን የጉዳት ደረጃ ለመገንዘብ መቻላቸውንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የተጀመሩ ጥረቶችን ማስቀጠል እንደሚገባ የጠቆሙት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎችም የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም አንስተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የተባቡሩት መንግስታት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ለማስቀጠል ዋና ጸሐፊው እና ሌሎች የድርጅቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋቸውን ገልጸዋል።

አያያዘውም የመንግስታቱ የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ጫናን ለማድረግ ያለሙ ተከታታይ ስብሰባዎችን ማካሄዱ አግባብነት የሌለው መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ሰላምን የማደፍረስ ተግባራትንም እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚደርግበትን ጫና በማቋቋም አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ መቻሉን ለምክትል ዋና ጸሃፊዋ አስረድተዋል።

ሰሞኑን የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባን በተሳካ ሁኔታ ተካሂዶ መጠናቀቁም በአብነትነት የሚጠቀስ መሆኑን ነው የገለፁት።

መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ውሳኔ ማሳለፉን፣ ሁሉን ዐቀፍ ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መከናወኑን እንዲሁም ከማንኛውም ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት መታቀቡ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች መሆኑን አስረድተዋል።

በሕወሓት የሽብር ቡድን በኩል ግን መጀመሪያውንም በሀገሪቱ አጠቃላይ የሰላም መደፍረስ እንዲኖር አቅዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ገልጸው አሁንም በሚያደርገው ትንኮሳ የእርዳታ አቅርቦት ተደራሽ እንዳይሆን ሆን ብሎ የማወክ ተግባሩ እንደቀጠለበት ነው ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ እንዲሁም በተካሄዱ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ሕዝብ የስብኣዊ እርዳታን የሚሻ መሆኑን ጠቅሰው መንግሥት በየብስም ሆነ በአየር በረራ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብም የሰብኣዊ እርዳታ በማቅረብ እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም ጥረቶችን በመደገፍ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በመጨረሻም መንግሥት ከተለያዩ አካላት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በማስቀጠል ተጨባጩን የኢትዮጵያ እውነታ የማስረዳት ተግባሩን አጠናክሮ የሚስቀጠል መሆኑን ለዋና ጸሃፊዋ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።