በማኦኮሞ ልዩ ወረዳ በአሸባሪው ሸኔ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ነጻ ማድረግ ተቻለ

የካቲት 1/2014 (ዋልታ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማኦኮሞ ልዩ ወረዳ በተካሄደ የተቀናጀ የሠላምና ፀጥታ ሥራ በአሸባሪው ሸኔ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ነጻ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ሙሳ ሃሚድ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ሸኔ ከሁለት ወራት በላይ በልዩ ወረዳው ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈጸም በንጹሃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

የሽብር ቡድኑን ጥቃት በመሸሽ በርካታ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉና የልዩ ወረዳውን አስተዳደር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በአሸባሪው ቡድን መውደማቸውን ገልጸዋል።

ቡድኑ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ የሚመላለሱ የሕዝብ እና የመንግሥት ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ንጹሃንን አግቶ በመውሰድ እንዲሁም ወደ ክልሉ የሚገቡ ነዳጅ፣ ሸቀጣሸቀጥ እና የምግብ እህል ሲዘርፍ እንደነበር ተናግረዋል።

በልዩ ወረዳው ቶንጎ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ጎሬ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በቡድኑ ተዘርፎ ስደተኞች ከአካባቢው መውጣታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የሀገር መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና የአባባቢ ሚሊሻ በቅንጅት ባደረጉት ዘመቻ አካባቢውን ከሽብር ቡድኑ ማጽዳት ተችሏልም ነው ያሉት፡፡

በተካሄደው የተቀናጀ የሠላምና ፀጥታ ሥራ 27 የሽብር ቡድኑ አባላት ሲደመሰሱ 35 ቆስለው መያዛቸውንና ሌሎች 13 ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል። የሽብር ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የጦር መሳሪዎች መማረካቸውን ጠቁመዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ የደረሰውን ጠቅላላ ጉዳት በመለየት መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግሥት እንቅስቀሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡