የኦሮሚያ ክልል ለሶማሌ ክልል የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

የካቲት 2/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡

ድጋፉን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተረክበዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ድጋፉን በኦሮሚያ ክልል ቦረናና ጉጂ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት መሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

በዚህም ለተደረገው ድጋፍ በክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ስም ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከክልሉ ብዙኃን መገናኛ ኤጄንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ሁለቱ ሕዝቦች በታሪክ ችግሮችን በጋራ ተቋቁሞ የማለፍ ልምድ እንዳላቸው ገልጸው በቀጣይም የሁለቱ አጎራባች ድንበር አካባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደር ሕዝቦችን በዘላቂነት ህወታቸውን የሚቀይሩ መለስተኛ የመስኖ ውሃ ፕሮጀክቶችን መገንባትና ማስፋፋት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።