የኦሮሚያ ክልል ለአማራ ክልል የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

የካቲት 3/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል በአማራ ክልል በአሸባሪው ሕወሓት ለደረሰው ጉዳት መልሶ ግንባታ የሚውል የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ሀገሪቱን የገጠሟት የአሸባሪው ሕወሓት የክህደት ወረራ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ይበልጥ እንድንበረታ እና እንድንተባበር አድርጎናል ብለዋል። ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል ባጋጠመው ድርቅ የአማራ ክልል ያደረገውን ድጋፍ አንስተዋል።

አሸባሪው ቡድን በሀገሪቱ ላይ ትልቅ ጠባሳ ያሳረፈ ጉዳት አድርሷል፤ ይህን በመቀልበስ ሀገር ለማስቀጠል እና ትውልድን ለማሻገርም መስዋዕትነት ተከፍሏል ብለዋል።

ከአንድነት ውጭ ያለው ሁሉ የውድቀት መንገድ ነው ያሉት ርዕሠ መስተዳድሩ የገጠመን ፈተና ወደ ላቀ መዳረሻ እንዲወስደን መደጋገፍን እንደምጠይቅ ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ርዕሠ መሰተዳድር የተመራው ልዑክ ያበረከተውን ድጋፍ የተረከቡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ለድጋፉ በክልሉ ሕዝብ ስም አመስግነዋል።

አሸባሪው ሕወሓት የመላ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ጠላት መሆኑን በማመን የአሸባሪውን ወረራ ለመመከት ሁሉም ርብርብ አድርጓል፤ ሀገሪቱም በጋራ በወደቁ ጀግኖች ልጆቿ ድልን ተቀዳጅታለች ብለዋል።

የተዋጉን ብዙ ኃይሎች ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አንድነት አሸናፊና ባለድል ቢያደርገንም ድሉን ዘላቂ ለማድረግ ሁለተኛውን ምዕራፍ በድል መቋጨትና በመልሶ መገንባቱም ድልን መቀዳጀት ይገባል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።