በደቡብ አፍሪካ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ11 ሺሕ ዶላር በላይ ድጋፍ ተደረገ

የካቲት 3/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ እና የአገር መከላከያ ሠራዊቱን ለማጠናከር በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር በደቡብ አፍሪካ ፑማላንጋ ፕሮቪንስ፣ በዊትባንክ እና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ከ11 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

በፕሪቶሪያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ የዳያስፖራ ተሳትፎ እና የኢሚግሬሽንና ቆንስላ ዘርፍ አስተባባሪዎች እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር ተወካዮች ተገኝተው ድጋፍ በማሰባሰቡ እንቅስቃሴ እና ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ለማኅበረሰቡና አስተባባሪ ኮሚቴዎች የዕውቅና እና የምስጋና የምስክር ወረቀትም ተሰጥቷል፡፡
የድጋፍ እንቅስቃሴው ሁሉንም ማኅበረሰብ በማሳተፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስተባባሪ ኮሚቴ አረጋግጧል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን መብታቸውን ለማስጠበቅና ክብራቸውን ለማስከበር፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትስስር ይበልጥ ለማጎልበት እንዲሁም በሌሎች የጋራ ማኅበራዊ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ በተሻለ አደረጃጀትና ቅንጅት ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ መንቀሳቀስ በሚያስችሉ አቅጣጫዎች ዙሪያ ምክክር መደረጉን ከውጭ ጉዳይ ሚሊስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡