ዘመቻ ‘በሙያዬ ለሀገሬ’ ተጀመረ

ዘመቻ ‘በሙያዬ ለሀገሬ’ ተጀመረ

የካቲት 3/2014 (ዋልታ) በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሆቴሎች እና የቱሪዝም መዳረሻዎች ዳግም ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ‘በሙያዬ ለሀገሬ‘ የተሰኘ ዘመቻ ተጀመረ።

በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ በሙሉና በከፊል ጉዳት ደርሶባቸው ከስራ ውጪ የሆኑ ሆቴሎችን እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመለየት ዳግም ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያስችል የበጎ ፍቃድ ዘመቻ ነው የተጀመረው።

የዘመቻው ጠንሳሽ የሆቴል አማካሪ ታሪኩ ሀይሉ ከአሸናፊ ሙሉጌታ እና ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ደብረብርሃን፣ ሸዋሮቢት፣ ከሚሴ፣ ከምቦልቻ፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ላሊበላ፣ ጭፍራና ካሳጊታ ከተሞች በዘመቻው የሚሸፈኑ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙትን ሆቴሎች እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማደራጀት ባሻገር የማማከር፣ የስልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግን የሚያካትት ዘመቻ መሆኑም ተነግሯል።

በበጎ ፍቃድ ዘመቻው እስካሁን 280 የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች በበጎ ፍቃደኝነት ለመሳተፍ የተመዘገቡ ሲሆን 80 የሚሆኑ የሆቴል አማካሪዎችም በኮሚቴ መልኩ ተዋቅረው ዘመቻውን እየመሩት ነው ተብሏል።

ለስራው ማስፈፀሚያ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ ታቀዶ እየተሰራ ሲሆን ለሆቴሎቹ የሚደረገውን ድጋፍ ለማሳደግም ቀጣይነት ያለው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር እየተከናወነ ነው ተብሏል።

በሀገሪቱ የሚገኙ የሆቴል ባለቤቶችና የዘርፉ ባለሙያዎችም ዘመቻ ‘በሙያዬ ለሀገሬ‘ን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቧል።

በትዕግስት ዘላለም