ሩሲያ በኢትዮጵያ የወደሙ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ እንደምታደርግ ገለፀች

የካቲት 3/2014 (ዋልታ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በኢትዮጵያ ከሩሲያ ፌዴሬሽን አምባሳደር ዬቭጌኒ ተረኪን ጋር በወደሙ የትምህርት ተቋማት መልሶ ማቋቋም ዙሪያ ውይይት አደረጉ፡፡

ሚኒስትሩ ባደረጉት ውይይት የሩሲያ ፌዴሬሽን ለረጅም ዓመታት በትምህርቱ ዘርፍ ያደረገውን እገዛና አስተዋጽኦ አድንቀው በትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታና በነፃ የትምህርት ዕድል ዙሪያ እገዛ እንዲያደረግ ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር ዬቭጌኒ ተረኪን በበኩላቸው የሁለቱ አገራት የትብብር ግንኙነት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረና በተለይ በትምህርቱ መስክ እየተሰራ ያለውን ግንኙነት በተጠናከረና በተስፋፋ መልኩ ለማስቀጠል መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡

አምባሳደሩ በተጨማሪ የትምህርት ተቋማትን መልሶ በማቋቋምና በመገንባት ሂደት ላይ አገራቸው እገዛ እንደምታደርግም አስታውቀዋል፡፡

የሩሲያ ፌዴሬሽን በያዝነው የ2014 ዓ.ም 38 የማስተርስና የፒኤችዲ የነፃ ትምህርት ዕድሎችን ከመስጠቱም በተጨማሪ በኒውክለር ኢነርጂ ኢንጂነሪንግ በማስተርስ ዲግሪ 10 የነፃ ትምህርት ዕድሎችን እንደሰጠ ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡