ከተማ አስተዳደሩ ለህገወጥ ተግባራት የተጋለጡ ከ400 ሺሕ በላይ ካርታዎች ማምከኑን አስታወቀ

ጥራቱ በየነ

የካቲት 4/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ አስተዳደር ለህገወጥ ተግባራት የተጋለጡ ከ400 ሺሕ በላይ ካርታዎችን ማምከኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ አስታወቁ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ወቅታዊ ጉዳይን መሰረት በማድረግ በመሬት ነክ ዙሪያ የሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲቆሙ አድርጎ መቆየቱን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት ህገወጥነትን መከላከል በጣም አስፈላጊ ስለነበር ነው ብለዋል።

በተለይም መሬት፣ ህንጻና ቤት ያላቸው አካላት ንብረታቸውን በመሸጥና በማሸሽ ለጦርነት ግብዓት እንዲውል በማድረግ ሽብርተኛውን ቡድን ሲደግፉ ተደርሶባቸዋል፤ አገልግሎቱ መቋረጡም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

‹‹አገር ጦርነት ውስጥ ስትገባና ሁሉም ሰው ትኩረቱ አንድ ነገር ላይ በሚሆንበት ጊዜ ያልተገባ የመሬት ወረራ ይፈጸማል፤ ይህንን ለመከላካል የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመስራትም አገልግሎቱን መዝጋቱ አስፈላጊ ነበር፤ በመሆኑም እነዚህን አግደን አሰራራችንን የመፈተሽ ተቋማቱን የማሻሻል ሥራ ተከናውኗል›› ብለዋል።

በዚህ አገልግሎት የማጥራትና የመፈተሽ ሥራ ውስጥም ቀደም ብለው ታትመው የነበሩ ከ4 መቶ ሺሕ በላይ የበርካታ ዓመታት ካርታዎች በሁሉም ክፍለ ከተሞች መገኘታቸውን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ እነዚህ ካርታዎች ህጋዊ ቢሆኑም ለህገ ወጥ ተግባር በየባለሙያው እጅና በየመደርደሪያዎች ላይ የተገኙ እንደሆኑና ሁሉም ካርታዎች እንዲወገዱ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል።

አሁን አገልግሎቱ የሚሰጠው የራሱ መለያ ቁጥር (ኮድ)፣ የመቆጣጠሪያ ሚስጥራዊ ቁጥር ባለው ካርታ ነው፤ ከዚህ በኋላ ካርታ የሚፈልጉ ሰዎችም ቀደም ያለውን ካርታ ይዘው ቢገኙ ህገወጥ መሆናቸውንም ማወቅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

አገር በዚህ መሰሉ የጦርነት ሂደት ውስጥ ሆና ህገወጥ ተግባርን የመከላከል ሥራ መስራት ከባድ መሆኑን የገለጹት ስራ አስኪያጁ ከተማ አስተዳደሩ ጸጥታ ከማስጠበቁ ጎን ለጎን በርካታ መሬቶችን ከወረራ ማዳን መቻሉን ጨምረው ተናግረዋል።

በመሬት ዙሪያ እየወጡ ያሉ መመሪያዎች ህገወጥነቱን እየተከላከሉ ነው ወይ? የጸጥታ አካላት እንዲሁም መዋቅሩ በሥራው ላይ የነቃ ተሳትፎን አድርጓል የሚለውን ለመለየት በ2013 ዓ.ም ሁለት ጊዜ የኦዲት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በተለይም ከለውጡ በፊት ከመሬት ጋር የተያያዙ ህገወጥነቶች ስር የሰደዱበት ሁኔታዎች እንደነበሩ በመረዳት በ2013 መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የኦዲት ሥራ አከናውኗል ብለዋል።

እንደ አቶ ጥራቱ ገለጻ በዚህም በ2013 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር የኦዲት ስራ በርካታ ሄክታር መሬት በግለሰቦች ተወሮ እንደነበር ለማረጋገጥ ተችሏል። አላግባብ የአርሶ አደሮችም መሬት ተይዞ እንደነበር ተረጋግጧል።

ይህንን መነሻ በማድረግም የተለያዩ የማስተካከያ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

በህገ ወጥ ሁኔታ የተያዙ ከ 2 መቶ 20 ሺሕ ካሬሜትር በላይ መሬቶች ወደመሬት ባንክ እንዲገቡ ሆኗል ያሉት አቶ ጥራቱ በጠቅላላው ከመሬት ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮች በመንግሥት ደረጃ ጠንከር ያለ ስራ እየተሰራባቸው ነው።

በቀጣይም ይህንን መሰል ህገወጥነት ለማስወገድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በመጨመር ሰፋፊ ስራዎች እንደሚሰሩ ማመልከታቸውን ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ መስራት እንዳለብን በማመን የተጀመሩ ስራዎች አሉ፤ ከዚህ ጎን ለጎንም መዋቅሩን በአዲስ መልክ አደራጅተን በመሬት ዙሪያ ይሰሩ የነበሩ ሦስት ተቋማትን ወደ አንድ እንዲመጡ ሆኗል።

በጠቅላላው የከተማ አስተዳደሩ በመሬት ዙሪያ የሚሰሩ ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል ጠንካራ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።