ግሎባል አሊያንስ በ10 ሚሊየን ብር በሎጊያ የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ ሊያካሂድ ነው

የካቲት 4/2014 (ዋልታ) ግሎባል አሊያንስ ግብረ ሰናይ ድርጅት በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ በአፋር ክልል ሎጊያ ከተማ የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ ሊያካሂድ መሆኑ ተገለጸ።

ድርጅቱ በሎጊያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ የማስፋፊያ ግንባታ ለመጀመር የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጧል።

እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምረው የሎጊያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ህይወት ሽመልስ እንደተናገሩት ትምህርት ቤቱ በአንድ ክፍል እስከ 120 ተማሪዎች በተጨናነቀ ሁኔታ እያስተማረ ይገኛል።

ትምህርት ቤቱ የመማሪያና አስተዳደር ክፍሎች ጥበት በተጨማሪ የውሃና የመጸዳጃ ቤት ችግሮች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው ይህ ችግር ተማሪ የመቀበል አቅሙን እንደገደበበት ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትውልድ ለመቅረጽ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ያለው የግሎባል አሊያንስ ቦርድ ሰብሳቢ አርቲስት ታማኝ በየነ የትምህርት ቤቱን ችግሮች ለመፍታት የድርጅቱን አባላት በማስተባበር በቀጣይ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግሯል።

የአፋር ክልል ሕዝብ ለአገሩ ያለውን ዘመን የማይሽረው ታማኝነት በተግባር አስተምሮናል ሲል አርቲስት ታማኝ ገልጿል።

የአፋር ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኑረዲን ሰዲቅ በበኩላቸው “ግሎባል አሊያንስና አርቲስት ታማኝ በየነ ከአፋር ሕዝብ ጎን በመቆም እያደረገ ያለው ሁሉን ዐቀፍ ድጋፍ የሚደነቅ ነው” ብለዋል::

የትምህርት ቤት የማስፋፊያው 8 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለሁለት ብሎክና የአስተዳደር ህንጻን ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን ያካትት መሆኑን ጠቅሰው ግንባታው በ8 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ለኢዜአ ገልጸዋል።