የአውራምባ ማኅበረሰብ ለትውልድ ዘመን ተሻጋሪ የሥራ ባህልን በማስተማር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተገለፀ

የካቲት 5/2014 (ዋልታ) የአውራምባ ማኅበረሰብ በ50 ዓመታት ጉዞ በአብሮነት እና በመከባበር እንዲሁም ችግሮችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ብሎም ለትውልድ ዘመን ተሻጋሪ የሥራ ባህልን በማስተማር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የማኅበረሰቡ መስራች ዙምራ ኑሩ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

የአውራምባ ማህበረሰብ 50ኛ ዓመት በዓል “ኑ ጠቃሚ እሴቶቻችንን በጋራ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው።

በአማራ ክልል የሚገኘው የአውራምባ ማኅበረሰብ የሥራ እኩልነትን በተግባር ያሳየ፣ ለሌሎች ማኅበረሰቦች ምሳሌ መሆን የቻለ እና ሁለገብ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ፈር ቀዳጅ ማኅበረሰብ መሆኑንም የማኅበሩ መስራች አመልክተዋል፡፡

የአውራምባ ማኅበረሰብ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ለመድረስ የተለያዩ ተግዳሮቶችን እንዳሳለፈ የ50ኛ ዓመት በዓል አከባበር ኮሚቴ ሰብሳቢ እናንየ ክብረት ገልፀዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ከመነሻው ይዞ የጀመረው “ትልቁ ሀብት ሰው ነዉ” በሚል በትልቅ ዓላማ የተነሳ ማኅበረሰብ በመሆኑ አሁንም ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር መፍታት የሚቻለው ልክ እንደአውራምባ ማኅበረሰብ አንድነትን በማጠናከር እና ትልቅ ሀብት ለሆነው ለሰው ልጅ ቅድሚያ መስጠት ሲቻል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በበዓሉ የአውራምባ ማኅበረሰብ እሴቶችና ተከባብሮና ተሳስቦ በጋራ የመኖር መንገዶች ለእውነተኛ እና ለዘላቂ ልማት ፋይዳው ምን ሊሆን ይችላል በሚል መነሻ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)ን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት