አካታች ብሔራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንፃር የምሁራንን ሚና የሚዳስስ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

የካቲት 5/2014 (ዋልታ) “አካታች ብሔራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንፃር የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የሠላም ሚኒስቴር ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለምን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታ ታየ ደንደአ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን እና ስትራቴጅ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዘውዱ እምሩን (ዶ/ር) እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል።

እንደ ሀገር በሠለጠነ መንገድ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መሻገርን መለማመድ እና ለትውልድም ማሻገር ይገባል ያሉት የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም የዜጎች ደኅንነት የተረጋገጠበት፣ ሠላም የሠፈነበት እና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ይገባል ብለዋል፡፡

ለትውልዱ አዲስ ምዕረፍ መክፈት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ ከጥላቻ ፍረጃና የተዛቡ ትርክቶች ወጥተን በሠለጠነ መንገድ መወያየት፣ ሀሳብና ልዩነትን ማክበር የሚቻልበት ሀገር እንዲሆን የተግባር ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ ምሁራን ለዚህ ስኬት ሚናቸው የጎላ መሆኑም ተገልጿል፡፡