ዓለም ዐቀፉ የሬዲዮ ቀን እየተከበረ ነው

የካቲት 6/2014 (ዋልታ) ዓለም ዐቀፉ የሬዲዮ ቀን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለ11ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው፡፡

ዕለቱን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር የቆዩት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ ትክክለኛ መረጃን በፍጥነት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ሬድዮ ኅብረተሰቡን በማንቃትና መረጃን ተደራሽ በማድረግ በኩል ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለመረጃ ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮች ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት በአገር ብሎም በህዝብ ሰላምና መረጋጋት ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ድርጊት በሕግ አግባብ ለማስተካከል ከሚደረገው ጥረት ባሻገር መገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ መረጃን በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡