በአማራ ክልል መደበኛ የልማት ሥራ ሊያሠራ የሚያስችል የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ መኖሩን ክልሉ አስታወቀ

የካቲት 7/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ በአንጻራዊነት የተረጋጋና ሰላም የሆነበት መደበኛ ሥራዎችን መሥራት የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በክልሉ የሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ጎንደርና ሌሎች አካባቢዎች በሕወሓት የሽብር ቡድን ተወረው በነበረበት ወቅት የሕዝቡ መሰረታዊ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ችግር ውስጥ ገብቶ እንደነበር ገልጸው በአሁኑ ወቅት ከውስን አካባቢዎች በስተቀር ነጻ ሆነው መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከወረራ ነጻ በሆኑ አካባቢዎች የልማትና መልሶ የማቋቋም ሥራ መሥራት የሚያስችል ሰላም መፈጠሩን የገለጹት ኃላፊው የተፈጠረውን አንጻራዊ የሰላም ሁኔታ የበለጠ በማረጋገጥ የልማት ሥራዎች የሚሰሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የአሸባሪው የትሕነግ ወራሪ ኃይል በነበረባቸው አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን ክልሉ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

የአማራ ክልል በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በመገምገም አስተማማኝ ሰላም በክልሉ ለማስፈን እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡