ጅማ ዞን በባሌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 11.4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

የካቲት 7/2014 (ዋልታ) የጅማ ዞን በባሌ ዞን ድርቅ ባስከተለው ችግር ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 11.4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ ለተጎጂ ወገኖች እንዲደርስ ትናንት በባሌ ሮቤ ከተማ በመገኘት ያስረከቡት የጅማ ዞን የአደጋ ስጋትና የልማት ተነሺዎች ጽ/ቤት ኃላፊ ሰለሞን ኤጄሬ እንዳሉት ድጋፉ የኦሮሞ ሕዝብ የተቸገረ ወገኑን የሚረዳበት የገዳ ሥርዓት አስተምህሮት አካል ነው።

ድጋፉ ኢትዮጵያዊያን በችግር ወቅት ያላቸውን የመረዳዳት የቆየ ባህል በተግባር ከማረጋገጥ ባለፈ ወንድማማችነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

ዞኑ ለድርቅ ተጎጂ ወገኖች ያደረገው ድጋፍ 11.4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው 3 ሺሕ 800 ኩንታል የምግብ እህል መሆኑንም አስታውቀዋል።

ችግሩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የጀመሩትን ሰብኣዊ ድጋፍ የዞኑን ሕዝብ በማስተባበር ቀጣይነት እንደሚኖረውም አረጋግጠዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱልሀኪም አልዪ በችግር ጊዜ ከጎናችን ለቆመው የጅማ ዞን አስተዳደር በተጎጂዎቹ ስም እናመሰግናለን ብለዋል።

በዞኑ ቆላማ የአርብቶ አደር ወረዳዎች ውስጥ ያጋጠመው ድርቅ ከባድ በመሆኑ ችግሩን ለመቀነስ እያደረገ የሚገኘውን ጥረት ሌሎችም አካላት እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

በዞኑ ስድስት ቆላማ ወረዳዎች ውስጥ 260 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች የክልሉ መንግሥት የአስቸኳይ የምግብ እህል እርዳታ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ አደጋ መከላከል እና የልማት ተነሺዎች ጽ/ቤት ኃላፊ ወንድማገኝ ከበደ ናቸው።

መንግሥት ድርቁ በሰው እና እንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ እያደረገ የሚገኘውን ጥረት ግለሰቦች፣ ተቋማት እና ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።