ሚኒስቴሩ በ7 ወራት 196 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

የካቲት 7/2014 (ዋልታ) የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት 7 ወራት 196 ቢሊየን 798 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ ላቀ አያሌው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ገቢው በርካታ ተግዳሮቶችን በማለፍ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።

በዚህም በተጠቀሱት ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 92 ነጥብ 45 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡

ገቢው ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር የ27 ቢሊየን 430 ሚሊየን ብር ወይም 16 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አንስተዋል፡፡

የተገኘው ገቢ ከሀገር ውስጥ ታክስ እና ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ የተሰበሰበ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የተሰበሰበው ገቢ በአገሪቱ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት አራት የተቋሙ ቅርንጫፎች ከሥራ ውጭ ሆነው፣ ከኮሮና ወረርሽኝ እና መሰል ተጨማሪ ችግሮች አንፃር ሲታይ ጥሩ አፈጻጸም መሆኑን አውስተዋል፡፡