በአማራ ክልል 11 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች የዕለት ደራሽ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል

የካቲት 9/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል በአሸባሪው ትሕነግ ወረራ እንዲሁም ከኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ጨምሮ 11 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች የዕለት ደራሽ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ።

ለእነዚሁ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች የፌደራል እና ክልሉ መንግሥታት፣ ዲያስፖራው፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠይቋል።

በክልሉ በአሸባሪው ትሕነግ ወረራ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው ከነበሩት ወገኖች መካከል አብዛኛዎቹ ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸውን የኮሚሽኑ ምክትል ኃላፊ እታገኘሁ አደመ ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ ከሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ እና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን በአጠቃላይ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ቆይተዋል።

በአሸባሪ ቡድኑ ወረራ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ከነበሩት ዜጎች መካከል አብዛኛዎቹ ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ከኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ቀደም ሲል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል የገቡ 900 ሺህ ወገኖች እስካሁን ወደ ቀደመ መኖሪያቸው ያልተመለሱ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥትም እስካሁን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ምክትል ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

ለእነዚህ ዜጎች የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው ጥሪ ያቀረቡት።