በኢትዮጵያ ነፃነታቸውን በተነፈጉ ዜጎች መብቶች ዙሪያ ምርመራ ሊካሄድ ነው

የካቲት 10/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ዙሪያ የመጀመሪያ ነው ያለውን ብሔራዊ ምርመራ ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ።

ብሔራዊ ምርመራው የመጀመሪያ እንደሆነ የተናገሩት የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ስልታዊና ውስብስብ የሆኑ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ያግዛል ብለዋል።

የምርመራው ተልዕኮ የህግ የበላይነትን በማስፈን ፍትህን በማረጋገጥ በኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብቶች ጥበቃና አከባበርን ማጎልበት ነው ተብሏል።

ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ብሔራዊ ምርመራውን ለማካሄድ የተቀረፀው ፕሮጀክት 15 ሚሊዮን ዩሮ ወጭ የሚደረግበት እንደሆነ እና ድጋፉ ከአውሮፓ ኅብረት መገኘቱን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በማረሚያ ቤቶች፣ በፖሊስ ጣቢያዎችና በእገታ ስር ያሉ ሰዎችን ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የመጎብኘት መብት እንዳለውም መገለጹን ኢብኮ ዘግቧል።