አዋሽ ባንክ የሞባይል ብርና የውክልና ባንክ አገልግሎት መተግበሪያን አስተዋወቀ

የካቲት 10/2014 (ዋልታ) አዋሽ ባንክ “አዋሽ ብር” የተሰኘ የሞባይል ብርና የውክልና ባንክ አገልግሎት መተግበሪያን ይፋ አደረገ።

የባንኩ ደንበኞች መተግበሪያውን በመጠቀም የሒሳብ እንቅስቃሴዎችን መከታተል፣ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ ከአዋሽ ብር ወኪሎች፣ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤቲኤሞች) ገንዘብ ወጪ ማድረግ፣ እንደትራፊክ ቅጣትና የትምህርት ቤት ክፍያ ያሉ የተለያዩ ክፍያዎችን እና ሌሎችንም ክንውኖች መፈፀም ይችላሉ ተብሏል።

የባንኩ ሥራ አስፈፃሚ ፀሃይ ሽፈራው እንደገለፁት ዘመኑ የደረሰበትን ዲጅታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም ባንኩ አሰራሩን እያዘመነ ይገኛል፡፡

በቀጣይም ከውጭ ባንኮች ጋር ለሚጠብቃቸው ብርቱ ፉክክር ተወዳዳሪ ለመሆን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የሞባይል መተግበሪያው በ6 ቋንቋዎች ማለትም በእንግሊዝኛ፣ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛና ሶማሊኛ የሚስራ ነው። መተግበሪያው በማንኛውም የስልክ ቀፎዎች ግልጋሎት ይሰጣል ተብሏል።

በሌላ ዜና ባንኩ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በ60 ሚሊዮን ብር የምግብ እህል ተገዝቶ እንዲሰጥ ቦርዱ መወሰኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

አዋሽ ባንክ ከተመሰረተ 27 ዓመታትን አስቆጠረ ሲሆን በመላ አገሪቱ ከ680 በላይ ቅርንጫፎች አሉት።

በተስፋዬ አባተ