የካቲት 12 የሰማዕታት ቀንን ያሰበ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው

የካቲት 11/2014 (ዋልታ) በነገው እለት 85ኛ ዓመቱ የሚታሰበውን የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው።

በፓናል ውይይቱ ላይ አባት እና እናት አርበኞችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻዎች ተገኝተዋል።

የፓናል ውይይቱን የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) “አባቶቻችን የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው የተረከብናትን ኢትዮጵያ ዛሬም ጠብቀናት ለትውልድ ልናሻግራት ይገባል” ብለዋል።

የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የታሪክ ተመራማሪው አበባው አያሌው በበኩላቸው ፋሽስት ጣሊያን ከጅምሩ አንስቶ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማንበርከክ ያደረገው ሴራ እና ኢትዮጵያዊያን የከፈሉትን መስዋዕትነት የተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ እያቀረቡ ይገኛሉ።

የካቲት 12 ቀን 1929 ፋሽስት ጣሊያን በሦስት ቀናት ብቻ ከ30 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያንን አዲስ አበባ ላይ በግፍ የጨፈጨፈበት ቀን በየዓመቱ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ታስቦ ይውላል።

በሜሮን መስፍን