በመተከል ዞን ከቀያቸው ተፈናቅለው ጫካ የነበሩ ከ3 ሺሕ በላይ ዜጎች ተመለሱ

የካቲት 11/2014 (ዋልታ) በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ በታጠቁ የሽፍታ ኃይሎች ጫና ከቀያቸው ተፈናቅለው ጫካ የነበሩ ከ3 ሺሕ 200 ተጨማሪ የጉሙዝ ማኅበረሰብ ክፍሎች ወደ ወረዳ ማዕከል ገቡ።

በክልሉ መንግሥትና በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ቅንጅታዊ ሥራ በርካታ ንፁሃን የጉሙዝ ማኅበረሰብ ክፍሎችን ከጥፋት ቡድኑ በመለየት ወደ ማዕከል እንዲገቡ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

በዳንጉር ወረዳ በሰሞኑ እየተከናወነ ባለው የኦፕሬሽን ሥራ ንፁሃን ዜጎችን ከጥፋት ቡድኑ በመለየት ድልሳንቢ ቀበሌ ላይ በተዘጋደው ማዕከል እንዲገቡ ተደርጓልም ነው የተባለው፡፡

የወረዳውን ሠላም ለማስከበር የተሰማራው የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ቅንጅታዊ ሥራ አሁን ላይ ከአዛርቲ ክትሊ፣ ከጊንፂ፣ ከአይፖፖ፣ ከደልሳንቢ እና ደቡህ ኮክል ቀበሌ ነዋሪዎችን ከጥፋት ቡድኑ መለየት እንደተቻለም ተጠቁሟል።

ከዚህ በፊት በተደረገው የሠላም ጥሪ 1 ሺሕ 485 ንፁሃን ሰዎች ማንቡክ ከተማ ላይ በተዘጋጀው ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ገብተው መሠረታዊ ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን የወረዳው መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።