“እስካሁን የተደረገ ድርድር የለም”ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአሻባሪው ትሕነግ ጋር በተያያዘ እስካሁኗ ደቂቃ የተደረገ ድርድር የለም ሲሉ አስታወቁ።

ድርድር ሲባል እሰማለሁ ግን እስካሁኗ ደቂቃ የተደረገ ድርድር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ማለት ግን እስከአካቴው ድርድር አይኖርም ማለት አይደለም ነው ያሉት።

ድርድር ቢኖር እንኳን ኢትዮጵያን ለማጽናት እንጂ ከዚያ ውጭ የሚሆን አካሄድ የለም ብለዋል። ትሕነግ ቀልብ ገዝቶ በድርድርና በሰላም አማራጭ ለመምጣት ከወሰነ ግን በበጎ ነው የምንወስደው በማለትም የሚሆነው ነገር ቢኖር ለሰላም ተስፋ መስጠት በሚል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ጥቅም የማይነካ እስከሆነ ድረስ መንግሥት ከየትኛውም አካል ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመወያይት በሩ ክፍት መሆኑን ነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያቸው ያነሱት።

በአገራዊ ምክክር መድረኩ ላይ ኮሚሽነሮቹ ስልጣናቸው ሁሉን አካታች የውይይት መድረክ መፍጠር እንጂ በኢትዮጵያ የትኛውም ነገር ላይ የሚወሰነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚያደርገው ሕዝበ ውሳኔ ነው ብለዋል።

ከአሸባሪው ትሕነግ ጋር በተያያዘ ታስረው የነበሩትን የእነስብሃት ነጋ መለቀቅ በተመለከተ 3 ዋነኛ ምክንያቶችን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደኛው ምክንያት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በሚል ነው ብለዋል። በእስረኞቹ መፈታት ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ወራት ከፍተኛ ጥቅም ተገኝቷል ብለዋል።

ሁለተኛው ምክንያት የታሳሪዎችን አጠቃላይ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ነው ያሉም ሲሆን ያልተፈቱ ብዙ የቡድኑ ሰዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

ሦስተኛው የተገኘውን ድል ለማስፋት እና የጦርነትን አስከፊነት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብለዋል። ሁኔታውና መጠኑ ይለያይ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ጠፍቶ አያውቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮ-ኤርትራን ለ3 ዓስርታት የዘለቀውን ጦርነትና ያስከተለውን ቀውስ ምሳሌ አድርገው አስረድተዋል።