የዓለም ጤና ድርጅት ለኦሮሚያ ክልል 31 ሜትሪክ ቶን የሕክምና ቁሳቁስ ደገፈ

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) የዓለም ጤና ድርጅት ለኦሮሚያ ክልል 31 ሜትሪክ ቶን መድኃኒቶችን፣ የሕክምና እቃዎችን እና የአልሚ ምግቦችን ድጋፍ አድርጓል።

ድርጅቱ ያደረገው ድጋፍ በቦረና ዞን በድርቅ እና በተለያዩ ወረርሽኞች የተጎዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመርዳት እንዲሁም በክልሉ የጨቅላ ሕፃናት የአልሚ ምግብ ፍላጎትን ለማሟላት የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ እና በዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት የሚታገዝ የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር እና ግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ ልዑክ በቦረና ዞን ጉብኝት ያደረገ ሲሆን በዞኑ በሚገኘው የዱብሉክ ጤና ማዕከልም ምልከታ አድርጓል።

ጉብኝቱ የኢትዮጵያ መንግሥት እና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት በቦረና ዞን ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ ለመስጠት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የክትትል እና ፈጣን ምላሽ፣ ሥነ ምግብ፣ የዋሽ፣ የክትባት እና የሎጂስቲክስ ባለሙያዎች በኦሮሚያ ክልል ላጋጠመው ድርቅ ለሚሰጠው ምላሽ ቀጥተኛ የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ኢብኮ የድርጅቱን ቲዊተር ገጽ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።