የካቲት 19/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በ200 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባውን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ህንጻ ሊያስመርቅ ነው።
ተቋሙ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የዜና ምንጭነቱን በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችለውን የህንጻ ግንባታ ማድረጉንም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ ተቋሙ የዜና ምንጭነቱን በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ለማስቀጠል ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
ተቋሙ ይገለገልበት የነበረውን ህንጻ የእድሳት ሥራ ተሰርቷል እንዲሁም ዘመናዊ የሆነ ስቲዲዮ ያለው ህንጻ ገንብቷልም ነው የተባለው።
ህንጻው አራት የሬድዮና ሶስት የቴሌቪዥን ስቲዲዮ የያዘ ሲሆን የህጻናት ማቆያም እንዳካተተ ተገልጿል።
ተቋሙ በአፍሪካ ቀዳሚ የዜና ምንጭ ለመሆን አቅዶ እየሰራ ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው አሁን ላይ ከሚሰራባቸው ቋንቋዎች በተጨማሪ ዓለም ዐቀፍ በሆኑ ተጨማሪ ቋንቋዎች ተደራሽ ለመሆን እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በቀጣይ የተቋሙን የ80 ዓመታት ጉዞን በተመለከተ የፓናል ውይይት ይደረጋል፣ ኤግዚቢሽንና ሌሎች መርሃ ግብሮች ይካሄዳሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በመላ አገሪቱ በ36 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ያለው ሲሆን ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ቋንቋዎች ለአገር ውስጥና ውጭ ሚዲያዎች የዜና ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በመስከረም ቸርነት