የካቲት 20/2014(ዋልታ) የካቲት 23 የሚከበረውን የዘንድሮ የዐድዋ ድል በዓል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።
የዘንድሮ የዐድዋ ድል በዓል “ዐድዋን ለኢትዮጵያዊያን ኅብረት፣ ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ” በሚል መሪ ቃል የሚከበር መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉን በደመቀ ሁኔታ በመላ አገሪቱ ለማክበር የሰላም ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞች ማኅበር፣ የቅርስ ባለሥልጣን፣ መከላከያ ሚኒስቴር እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት የተካተቱበት ዐቢይ ኮሚቴ፣ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን የአገር ውስጥ ምሁራን የሚሳተፉበት ሲምፖዚየም እንዲሁም የውጭ ዲፕሎማቶችን እና ዲያስፖራውን የሚያሳትፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሲምፖዚየምም እንደሚኖርም አመልክተዋል።
ኤግዚቢሽኖች እና የስፖርት ኩነቶች መዘጋጀታቸውንም ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ የፈረስ ትርዒቶችም የበዓሉ ድምቀቶች እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
እንደኢፕድ ዘገባ በዓሉ በክልል ደረጃም ተመሳሳይ ዝግጅት ተደርጎ እንደሚከበርም ጠቁመዋል።
ከአዲስ አበባ መስተዳድር እና ኦሮሚያ ክልል ጋርም አዲስ አበባ የሚከበር በመሆኑ አንድ ላይ በመቀናጀት ለማክበር በጋራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዐድዋ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያንም ትልቅ በታሪክ የተመዘገበ ድል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ የዐድዋ ጦርነት በተደረገበት ወቅት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት ወደ አፍሪካ ተስማምተው የዘመቱበት እና አብዛኛዎቹን የአፍሪካን አገሮች በቀላሉ መቆጣጠር የቻሉበት ቢሆንም በኢትዮጵያ ያልጠበቁትን ሽንፈት ተከናንበው የተመለሱበት መሆኑን አስታውሰዋል።
የተገኘው ድል በወቅቱ ኢትዮጵያ ተመጣጣኝ የጦር መሳሪያ ባትታጠቅም ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የዳበሩ የውጊያ ስልቶች እና በሌሎች ዘንድ ያልተለመደውን የፈረስ ውጊያ ስልቶችን በመጠቀም የተገኘ ትልቅ ድል መሆኑን ጠቁመዋል።
ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸውን ልምድ እና ችሎታ በመጠቀም በጋራ እና በአንድነት ቆመው ጦርነቱን ማሸነፍ ችለዋል ብለዋል።
ወጣቱ ከዐድዋ ድል አገር ወዳድነትን እና ለአገር ነጻነት መቆምን መማር አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
ዐድዋ በትልቅ መሥዋዕትነት በርካታ ኢትዮጵያዊያን የጦር መሪዎችን ጨምሮ ተሠውተውበት የተገኘ ድል መሆኑን መረዳት ይኖርበታልም ብለዋል።
ከዐድዋ በመማር ወጣቱ በቆራጥነት አገሩን መጠበቅ እና መከላከል እንዳለበት ጠቁመው በዓሉን ወጣቱና ሁሉም ሕዝብ በነቂስ በመውጣት እንዲያከብርና ለበዓሉ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽንም እንዲጎበኝ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።