በአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት የዓድዋን ድል የሚዘክር አውደ-ርዕይ ተከፈተ

የካቲት 21/2014 (ዋልታ) በአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የዓድዋን ድል የሚዘክር አውደ-ርዕይ ለሕዝብ ተከፈተ።
አውደ-ርዕዩ ከዛሬ የካቲት 21 እስከ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ይሆናል ተብሏል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ እንደገለጹት በአወደ-ርዕዩ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች በዓድዋ ለአገር ነጻነት የከፈሉትን ዋጋ ይዘክራል።
በአውደ-ርዕዩ ላይ የዓድዋን ጀግኖችን የሚዘክሩ ስዕሎች፣ ፎቶግራፎችና የተለያዩ ተጨባጭ ታሪካዊ ቅርሶች በስፋት እንደሚቀርቡም ነው የገለጹት።
እነዚህ ስዕሎችና ፎቶግራፎች ወጣቱ ትውልድ የዛሬይቷ ኢትዮጵያ እንዴት እንደቆመችና የድሉንም ትክክለኛ መረጃ ለማወቅ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
ይህም ኅብረተሰቡ የዓድዋን ድል በተመለከተ ያለውን መረጃ ለማስፋት እንደሚጠቅም ገልጸው በዘርፉ ጥናት ለሚያድርጉ አካላትም ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።