ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ጀግኖች አባቶቻችን በክብር ያቆዩልንን አገር በቀላሉ ለማፍረስ የሚጥሩ አካላት የአድዋን ድል ምንነት ያልተገነዘቡ ናቸው አሉ

የካቲት 22/2014 (ዋልታ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ጀግኖች አባቶቻችን በክብር ያቆዩልንን አገር በቀላሉ ለማፍረስ የሚጥሩ አካላት የአድዋን ድል ምንነት ያልተገነዘቡ ናቸው አሉ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ 126ኛውን የአድዋ ድል በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የመላው ኢትዮጵያዊያን የጀግነነት፣የአልገዛም ባይነት ምልክት፣የጥቁር ህዝቦች አለኝታ የሆነውን የአድዋ በኣል ስናከብር የቅኝ ገዥዎችን እብሪት የሰበረ፣በተቃራኒው የቅኝ ተገዥዎችን የነጻነት ትግል ከጫፍ እስከ ጫፍ ያነቃነቀ የእኛ ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ ነው።

ዘንድሮ ለ126ጊዜ በልዩ ሁኔታ አድዋን ስናከብር  እኛም እንደ ቀደምት አባቶቻችን ታላቅ ሀገርና ህዝብ ለመመስረት ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል!

ከዛሬ 126 ዓመት በፊት በአድዋ ተራሮች  የፈሰሰ ደም፣የተከሰከሱ አጥንቶች ለሀገር ክብርና ሉኣላዊነት መሆኑን ማንም የሚዘነጋው አይደለም።

የሀገር ነጻነት፣ የህዝቦች አልገዛም ባይነት ትልቅ ማሳያ ነው።

እንደ ያኔዎቹ ቅኝ ገዢዎች ሁሉ አሁንም ኢትዮጵያ ሀገራችንን ለማፍረስ፣ ህዝቧን ለእርስ በርስ እልቂት ለመዳረግ የሚታትሩ የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን በርካቶች ናቸው።

ባለፉት ጥቂት አመታት ያየናቸው ፈተናዎች ይህን ሀቅ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።

ያም ሆኖ ጥንትም ሆነ የአሁኑ ትውልድ የሀገሩን ሉኣላዊነት መደፈር ከሚያይ ሞቱን ይመርጣል።

ጀግኖች አባቶቻችን ያቆዩትን ሀገር አሁን ላለው ትውልድ ለማስተላለፍ የደምና የአጥነንት መስዋዕትነት ከፍለዋል።

ይህ መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም ከአድዋ ድል የአልሸነፍ ባይነት ጥልቅ የሀገር ፍቅር ጎልቶ ይታያል።

ጀግኖች አባቶቻችን በክብር ያቆዩልንን ሀገር በቀላሉ ለማፍረስ የሚጥሩ አካላት ምናልባትም የአድዋን ድል ምንነት ያልተገነዘቡ ናቸው።

ዛሬ በልበ ሙሉነት ሀገር አለን ብለን መናገር እንድንችል ላደረጉን ጀግኖች አባቶቻችን ክብር ይገባቸዋል።

የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን አደራ ተረክቦ ይህችን ሀገር ለማስቀጠል የደም እና የአጥንት መስዋዕትነት እየከፈለ ነው።

ጠላት የከፈተብንን ወረራ መክተን ፊታችንን ወደ ልማት እያዞርን ነው።

ፈተናዎቻችንን ፊት ለፊት እየተጋፈጥን በሁሉም ዘርፍ ድል በመጎናጸፍ ላይ እንገኛለን።

ያጋጠሙን ፈተናዎች ይበልጥ ጥንካሬ ሰጡን እንጂ እንድንሸነፍ አላደረጉንም።

መላው ኢትዮጵያውያን በአንድ ድምጽ ሆ ብለው በመነሳት የጠላትን ሴራ በማክሸፍ ደማቅ ታሪክ አስመዝግበዋል።

አሁንም የጠላትን ፍላጎት እየገታን ወዳለምነው የብልጽግና ጉዞ እንሻገራለን።

ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆነን እንኳ ልማታችንን እያስቀጠልን ነው።

እኛ ከተባበርን እና አንድነታችንን ካጠናከርን የሀገራችንን ስምና ክብር ከፍ በማድረግ ድህነታችንን ታሪክ ማድረጋችን አይቀርም።

ለመላው ለሀገራችን እና ለክልላችን ህዝቦች በድጋሚ እንኳን ለአድዋ የድል በአል በሰላም አደረሰን ለማለት እወዳለሁ።