በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 34.5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

የካቲት 23/2014 (ዋልታ) የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን በሶማሌ ክልል በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች 34 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በመሆን ወደ ጅግጅጋ ያመሩት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ አስረክበዋል።

የዓይነት ድጋፉ በኮንትሮባንድ የተያዙና ግምታቸው 22 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሆነ ልዩ ልዩ አልባሳት፣ 25 ተሽከርካሪ የእንስሳት መኖ፣ 716 ኩንታል ምግብ እንዲሁም ፍራሽና ብርድ ልብስን ያጠቃለለ ነው ተብሏል።

ከዓይነት ድጋፉ በተጨማሪ ተቋማቱ የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በጥሬ ገንዘብ ማስረከባቸውን ከሶማሌ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው ሌሎች አካላትም የድርቁን ስፋት በመረዳት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡